ከመስዋት የሚበልጥ (በኑሮ የሚገለጥ አምልኮ)

...በኑሮ የሚገለጥ አምልኮ በህልውናው ውስጥ ለሚደረግ የግንኙነት አምልኮ መሠረት ነው። የግ ንኙነት አምልኮ በኑሮ ለሚገለጠው አምልኮ ጉልበት የሚሰጥ ነው...
በምዕራፍ አንድ ላይ ስለ አምልኮ ስንነጋገር በግንኙነት የሚገለጥና በኑሮ የሚገለጥ አምልኮ በሚል ትርጉም መስጠታችን ይታወሳል። እስከ አሁንም ባሉት ምዕራፎች ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በምናደርገው ግንኙነት ውስጥ አምልኮተ መስዋዕት ምን ያህል ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተመልክተናል። ሆኖም ግን ከምናቀርብለት ምስዋዕት ይልቅ የሚያስቅድማቸው እና የሚያስበልጣቸው ደግሞም በእኛ ላይ ሊያያቸው የሚወዳቸው እንገብጋቢ ጉዳዮች አሉ። ቦታ ለሚሰጠው ቦታ መስጠት፣ የሚያከብረውን ማክበር፣ የሚንቀውን መናቅ መቻል በእግዚአብሔር ዘንድ መስዋዕታችን ደስ የሚያሰኝና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ያደርግልናል።
በኑሮ የሚገለጥ አምልኮ በህልውናው ውስጥ ለሚደረግ የግንኙነት አምልኮ መሠረት ነው። የግ ንኙነት አምልኮ በኑሮ ለሚገለጠው አምልኮ ጉልበት የሚሰጥ ነው። ለምሳሌ ራስን መካድ የምንማረው በኑሮ ውስጥ ከራስ ጋር በሚደረግ ትግል ሳይሆን በህልውናው ውስጥ በመቆየትንና ራሱን አሳልፎ በመስጠት ራስን መካድ ክሚያስተምረው አምላክ ጋር አብሮ በማሳለፍ ብቻ ነው።
በሌላ መልኩ ደግሞ በኑሮአችን እግዚአብሔር የሚከብርበት አካሄድ ሳይኖረን በህልውናው ውስጥ ብናመልከው አምልኮአችን ተቀባይነት አይኖረውም። ስለሆነም በየግዜው ማንነታችንን እንድንፈትሽባቸውና ራሳችንን እንድንመዝንባቸው ስለሚያደርጉ ከመስዋዕት ስለሚበልጡ መለኮታዊ መስፈርቶች ማየቱ ተገቢ ይሆናል። እነዚህም መታዘዝ፣ ምህረት ማድረግ፣ እግዚአብሔርን ማወቅ፣ የተሰበረ ልብ መያዝና ፅድቅንና ቅን ነገርን ማድረግ ናቸው።

ሀ. መታዘዝ ከመስዋዕት ይበልጣል

' እነሆ መታዘዝ ከመስዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።'

ይህ ቃል በእስራኤል ላይ የመጀመሪያ ንጉስ ለነበረው ለሳኦል የተነገረ ቃል ነው። አማሌቃውያንን ፈፅሞ እንዲያጠፋና እንዲበቀል ከእግዚአብሔር ዘንድ በሳሙኤል በኩል ትዕዛዝ የደረሰው ሳኦል ለአማሌቅ ንጉስ ለአጋግና ለተመረጡት በሬዎች፣ ለሰቡትም በጎች በመራራቱና እግዚአብሔር በጨከነበት ጉዳይ ላይ መጨከን ባለመቻሉ ምክን ያት መንግስቱ ከእርሱ ተቀደደ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ተናቀ።
መታዘዝ ያልተጓደለን ምልዕክት፣ በትክክለኛ ጊዜ ወደ ትክክለኛ ቦታ ማድረስ ማለት ነው። ከእነዚህ ከሶስቱ አንዱ ካልተፈፀመ መታዘዝ ሙልዓትን አያገኝም።
የሳኦል መታዘዝ የተጓደለ መልዕክት የያዘ ነበር ምናምንቴዎቹንና የተናቁትን ሁሉ ፈፅሞ ቢያጠፉም ነገር ግን የተመረጡትንና የሰቡትን በማስቀረቱ ምክን ያት የተሰጠውን “ሁሉን ፈፅሞ የማጥፋት መለዕክት” ተላልፎአል። የመታዘዝ መንፈስ የሌላቸው ሰዎች ሁልጊዜ በቂ ምክንያት ያቀርባሉ አልያም በሌሎች ላይ ጥፋታቸውን ያላክካሉ። ሳኦል ያቀረበው በቂ ምክንያት በህዝቡ ጥያቄ መሠረት የሰቡትን ከብቶች ለእግዚአብሔር ሊሰዋ እንዳስቀራቸው የሚያስምስል ነበር።

ሳኦል በትክክለኛ ጊዜ አልታዘዘም

“ ሳኦልም፦ ህዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደተበታተኑ፣ አንተም በቀጠሮው እንዳልመጣህ፣ ፍልስጤማውያንም ወደ ማክማስ እንደተሰበሰቡ አየሁ። . . . ስለዚህ ሳልታገስ የሚቃጠል መስዋዕትን አሳረግሁ፡ አለ። “

በሳሙ ኤል ሊቀርብ ይገባው የነበረው መስዋዕት ለተቀጠረበት ሰባተኛ ቀን ፍፃሜ ትንሽ ሰዓታት ቀርቶት ነበር። ሆኖም ግን ሳኦል መታገስ አቅቶት በራሱ መስዋዕትን ማሳረጉ የመታዘዝን የጊዜ ቀመር የተላለፈ ለመሆኑ በቂ ማስረጃ ነው። ለዚህም ደግሞ የሳሙኤልን መዘግየት፣ የህዝቡን መበታተንና የፍልስጤማውያንን ለጦርነት መሰብሰብ እንደ ምክንያት ሲያቀርብና ራሱን ትክክለኛ ለማድረግ ሊሞክር እንጂ ጥፋቱን ተቀብሎ ይቅርታን ሲጠይቅና ምህረትን ሲለምን አናየውም። ስህተታቸውን አለመቀበል የማይታዘዙ ሰዎች አይነተኛ መገለጫ ነውና።
ሳኦል ወደ ትክክለኛ ቦታ መልዕክቱን አላደረሰም

“ ሳኦልም፦ ዳዊትን ከግ ንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለው ብሎ ጦሩን ወረወረ። “

አንዳንድ ሰዎች ዳዊት ከሳኦል ይልቅ ሃጥያትን ሰርቶአል ብለው ያስተምራሉ። ምክን ያቱም ዳዊት ቤርሳቤህን ስለወሰደና ባልዋን ኦሪዮንን ስላስገደለ። በእርግጥ ይህ የከፋ ሃጥያት ነው። ነገር ግን የተቀባውን ዳዊትን በየምድረበዳው እና በየዋሻው ማሳደዱ፣ ለመግደል መሞከሩና ደጋግሞ ጦር መወርወሩ ሳኦልም የባሰ ነፍሰ ገዳይ መሆኑን የሚያረጋግጥልን ማስረጃ ነው። እግዚአብሔር ንጉስ አድርጎ በእስራኤል ላይ ሲሾመው የህዝቡን ጠላቶች እንዲያጠፋና በእጁ ያለውን ጦር ጎልያድን በመሰሉት የጠላት ሃያላን ላይ እንዲያውል በዘመኑ ሁሉ እግዚአብሔርን የመፈለግ አርዓያና የመሲሁ የዘር መንገድ የነበረውን ዳዊትን እንዲገድል አልነበረም። በመሆኑም የተሰጠውን ሃላፊነት የሞላበትን ትዕዛዝ ትክክለኛ ቦታ ወደነበሩት ጠላቶች አላደረም።

ከምናቀርብለት ምስጋናና ዝማሬ ይልቅ እግዚአብሔር እንድንታዘዘው ይፈልጋል። መታዘዝ የጎደለው አግልግሎትም ሆነ መስዋዕት ተቀባይነትን ከማጣቱም በላይ ተራፊምን እንደማምለክና ምዋርተኛ የመሆንን ያህል ይቆጠራል። ከመታዘዝ የሚጀምር መስዋዕት ግን ለበረከትና ለድል ህይወት የሚያጋልጥ ነው።

“ እሺ ብትሉ ለእኔ ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላቹ ። “

እምነት፣ ፍቅርና እግዚአብሔርን መፍራት መታዘዝ እንድንችል የሚያግዙንና በመታዘዝ ሂደትም ውስጥ ቁልፍ ሚናን የሚጫወቱ መንፈሳዊ ሀብቶች ናቸው። ከእምነት የሚነሳ መታዘዝ

“በእርሱም ስለ ስሙ በአህዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሳ መታዘዝ እንዲገኝ ፀጋንና ሐዋሪያነትን ተቀበልን። “

የአብርሃም መታዘዝ የመነጨው እግዚአብሔርን ከማመኑ ውስጥ ነው። የሚያምን ሰው አድርግ የተባለውን ለማድረግ፣ ሂድ ወደተባለው ስፍራ ለመሄድ፣ ስጥ የተባለውን ለመስጠት አይቸገርም። ምክንያቱም አስቀድሞ በእምነት አይኑ ስለሚያይ እና ተስፋውን ስለሚጨብጥ ነው።
ከፍቅር የሚነሳ መታዘዝ

“ብትወዱኝ ትዕዛዜን ጠብቁ። “

ከመውደድ የሚመነጭ መታዘዝ የአዲስ ኪዳን መመሪያ ነው። ከልባችን የምናፈቅረውን ሰው ማሳዘን አንፈልግም። አድርጉ የሚለን ነገር ባይመቸን እንኳ ያንን ሰው ከመውደዳችን የተነሳ ሁሉን እናደርጋለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእርሱ ካለን ፍቅር አመንጭተን እርስ በእርስ የመዋደድን ትዕዛዝ እንድንፈፅምለት ይፈልጋል። አጠገባችን ያለውን ሰው ሳንወድ የማናየውን አምላክ ለናመልክና ለንወድ አንችልምና።
ከፈሪሃ እግዚአብሔር የሚነሳ መታዘዝ

“ እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል።”

እግዚአብሔርን መፍራት ያለማንገራገር መታዘዝን የወልዳል። ይህም ፍርሃት ቅጣትን ካለመውደድ ሳይሆን አክብሮት ከተሞላበት ማንነት ( Reverence) የመነጨ ነው። ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ሰው ፈቃዱን ለማድረግና ለመታዘዝ ፈፅሞ አይቸገርም። ምክንያቱም በመታዘዙ ከሚደርስበትና ከሚያልፍበት ችግር ይልቅ ትዕዛዝ የሰጠውን አምላክ መፍራት ይመርጣል። ስናጠቃልለው ከእምነት የሚነሳ መታዘዝ ለሚመጣልን ትዕዛዛዊ ድምፅ ምላሽ ሊያሰጥን፣ ከፍቅር የሚዋጥዐ መታዘዝ ህግን (ትዕዛዝን) እንድንፈፅም ያደርገናል፣ ከፈሪሃ እግዚአብሔር የሚወጣ መታዘዝ ደግሞ ሃጥያትን እንዳናደርግ፣ እንቢ እንድንል ያስችለናል ማለት ነው።

2. የተሰበረ ልብ ከመስዋዕት ይበልጣል

መስዋዕትን ብትወድስ በሰጠሁህ ነበር፣ የሚቃጠለውንም መስዋዕት ደስ አያሰኝህም። የእግዚአብሔር መስዋዕት ደስ አያሰኝህም። የእግዚአብሄር መስዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።”

ይህ መዝሙር ዳዊት ወደቤርሳቤህ ከገባ በኃላና ባልዋን ኦርዮንን ካስገደለ በኃላ ነብዩ ናታን ወደእርሱ ምመጥቶ በእግዚአብሔር ቃል ስለሃጥያቱ በነገረው ጊዜ የዘመረው ነው። ብዙ መስዋዕትን በማቅረብ የታወቀው ዳዊት በእግዚአብሔር ዘንድ አስፀያፊ የሆነውን ሃጥያት ባደረገ ጊዜ በዚያው ማንነቱ የሚቃጠል መስዋዕትን ለማቅረብ አልደፈረም። ይልቁንም መንገዱን ለማስተካከልና የተሰበረን ልብ ለመያዝ ውስጡን እንዲያድስለት ለአምላኩ የንስሃን ፀሎት አቅርቦአል። ዳዊት በሶስት አቅጣጫ መንፈሱ እንዲታደስለት ሲጠይቅ እናየዋለን፦ በቀና መንፈስ ፣ በእሽታ መንፈስና በተሰበረ መንፈስ። እነዚህ ሶስት የሰው መንፈስ እድሳቶች ሃጥያት በሰራን ጊዜ ሳኦል በተናቀበት መልኩ እግዚአብሔር እንዳይንቀን የሚያደርጉ ለባችንን የምናስተካክልባቸው መንገዶች ናቸው። የተሰበረ መነፈስ ሃጥያትን መናዘዝን፣ ምህረት መጠየቅንና መንገድን ለማስተካከል ቃል መግባትን እንደሚያጠቃለለ ከመዝሙሩ ጠቅላላ ሃሳብ እንረዳለን።

3. ምህረት ማድረግ ከመስዋዕት ይበልጣል

“ ምህረትን እወዳለው መስዋዕትን አይደለም። “

ምህረት በአንድ መልኩ ተበድለን ሳለ ይቅርታ ማድረግን ሲያመለክት በሌላ መልኩ ደግሞ ለሌሎች ቸርነት የተሞላበትን መልካም ምግባር ያሳያል። ምህረት መስዋዕት ስናቀርብ ብቻ የምናስበው ጉዳይ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ልናሳየው የሚገባን መንፈሳዊ ልምምድ ነው። እግዚአብሔርም በዝማሬአችን ሆነ በምስጋናችን ከምናቀርበው መስዋዕት ይልቅ ምህረት ማድረግን በተግባር እንድንገልጠው ይሻል። በእርግጥ ተበድለን እያለ ይቅርታ ማድረግ እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግ ን ይቅር ካላልን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነ ከሰዎች ዘንድ ይቅርታን ማግኘት ስለማንችል ሁሉም ሰው በሚያልፍበት በዚህ ይቅር የማለት ጎዳና ላይ መራመድ የግድ ይሆናል።

“ እንግዲህ መባህን በመሰዊያው ካይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ እንዳች በአንት ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሰዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወምድምህ ጋር ታረቅ በኃላም መባህን አቅርብ።”

በመሠረቱ ይህ ክፍል የሚያወራው ስንበደል ይቅርታ ስለማድረግ ሳይሆን እኛ የበደልነው ሰው ካለ፣ ወይም በእኛ ቅር የተሰኘ ሰው ካለ መስዋዕታችንን አቁመን አስቀድመን ይቅርታ በመጠየቅ እርቅን ስለመፍጠር ነው። ስለዚህ በሁለቱ ይቅርታን በመስጠትና ይቅርታን በመጠየቅ አቅጣጫዎች ራሳችንን መገምገምና መፈተሽ ብሎም እንደ እግዚአብሔር ቃል ሁኔታዎችን ማስተካከል ለምናቀርበው መስዋዕት ተቀባይነት ቁልፍ ሚናን ይጫወታል።

4. እግዚአብሔርን ማወቅ ከመስዋዕት ይበልጣል

“ ከመስዋዕት ይልቅ ምህረትን፣ ከሚቃጠል መስዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለሁና።”

በመረጃ ደረጃ ብቻ ያለ ዕውቀትና ህብረት ከማድረግ የሚገኝ ዕውቀት ፈፅሞ የተለያዩ ናቸው። ስለ እግዚአብሔር ማወቅ ያስታብያል፣ እግዚአብሔርን ማወቅ ግን ትሁት ያደርጋል። በሌላ አባባል ቃሉን በአእምሮ ብቻ ማወቅ ያስታብያል፣ ቃሉን መኖርና ማድረግ ግን ትሁት ያደርጋል። መስዋዕት ከምናቀርብለት ይልቅ እግዚአብሔር እርሱን ለማወቅ በሚኖረን ፍላጎት ይደሰታል።
እውቀት ሶስት ዋና ደረጃዎች አሉት፦
እውነተኛ አምልኮ እውነተኛ እውቀትን ይጠይቃል። ጌታችን ኢየሱስ ለሰማሪያይቱ ሴት የነገራት ቃል ይህንኑ ያረጋግጥልናል።

“ እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላቹ ፣ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን።”

መስገድ ወይም ማምለክ መቻላችን እግዚአብሔርን ለማወቅ ማረጋገጫ አይደለም። ሳሙኤልም ገና ብላቴና ሳለ እግዚአብሔርን ሳያውቅ ያገለግል ነበር። ስለዚህ ከመስገዳችንም ሆነ ከማገልገላችን በፊት የምንሰግድለትንና የምናገለግለውን አምላክ ከመረጃና ከመተዋወቅ ( እንደግል አዳኝ አድርጎ ከመቀበል) ባለፈ መልኩ ህብረት ከማድረግ በሚገኘው የዕውቀት ደረጃ ልናውቀው ይገባል። ሆኖም ግን ከህብረት የሚገኘው እውቀት መጨረሻ የሌለውና ለዘላለም አውቀነው የማንጨርሰው ነው፣ እግዚአብሔር ከመታወቅ ሁሉ ያልፋልና። በመሠረቱ እግዚአብሔርን ባወቅነው ቁጥር ስለ እርሱ የማናውቃቸው እጅግ ብዙ ነገሮች እንዳሉ እየተረዳን እንሄዳለን።

“ እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን፣ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ህይወት ናት።”

5. ፅድቅንና ቅን ነገርን ማድረግ ከመስዋዕት ይበልጣል

“ እግዞአብሔር ከመስዋዕት ይልቅ ፅድቅንና ቅን ነገርን ማድረግ ይወድዳል።”

በዚህ ክፍል መሠረት ፅድቅ የሚለው ቃል የሚያመለክተው በክርስቶስ በማመን የሚገኘውን ፅድቅ አይደለም፣ ትክክለኛ የሆነን ነገር ማድረኝ እንጂ፤ ህሊና ደግሞ በሰው ልጆች ሁሉ ውስጥ የተቀመጠ የትክክለኛ ነገር መለኪያ መስፈርት ነው። ስለዚህ ፅድቅ ከዚህ ህሊና ጋር አብሮ የሚሄድና በኑሮ የሚገለጥ ትክክለኛ ድርጊት ነው። ይህም ከእውነተኛና ከንፁህ ህሊና የሚወጣ ትክክለኛ ድርጊት በእግዚብሔር ቃል ተፈትኖ ያለፈ መሆን ይገባዋል። ስለዚህ ህሊናችን ለማይወቅሰን እውነት መኖርና ቅን የሆነውን ነገር ማድረግ ከመስዋዕት ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ብልጫ ያለው የህይወት ዘይቤ ነው።
ሆኖም ግን አንድ ሰው በፅድቅ ሲኖርና ቅን ነገርን ብቻ ሲያደርግ የሚያጋጥመው ፈተና ቀላል አለመሆኑን አጥብቀን መረዳት ይኖርብናል። ምክንያቱም የሚያልፍባቸው መንገዶቹና አካሄዶቹ ሁሉ እጅግ ዋጋ የሚያስከፍሉት ሊሆኑ ይችላሉና። የቃየን መስዋዕት ተቀባይነትን ያጣው ትክክለኛና ቅን የሆነውን ነገር ማድረግ ባለመቻሉ ነው።

“መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን?”

ቅን ነገርን ማድረግ በስራና በንግድ ቦታ፣ በቤትም ሆነ በውጪ ከሰዎች ጋር ባለ ህብረት፣ በአሰሪና በሰራተኛ መካከል ባለ የስራ ግንኙነት ሁሉ የሚገለጥ የኑሮ መስዋዕት ነው። ይህም መስዋዕት ለሌሎች በመኖር፣ የራስን ጥቅም በመተውና ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ በመሰጠት የሚገለፅ ነው።

6. መውደድ ከመስዋዕት ይበልጣል

“ በፍፁም ልብ በፍፁም አእምሮም በፍፁም ነፍስም በፍፁም ሃይልም እግዚአብሔርን መውደድ ባልንጀራንም እንደራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መስዋዕትና ከሌላው መስዋዕት የሚበልጥ ነው።”

ፍቅር ወይም መውደድ የመንፈሳችን ክፍል ከሆነው ከልባችን ይጀምር እና በነፍሳችን አእምሮ አልፎ በአካላችን በሚገለፅ ሙሉ ሃይል የሚታይ እንድሆነ ከክፍሉ እንረዳለን። ይህም ፍቅር አስቀድሞ ለእግዚአብሔር ከዚያም ለራስና ለባልንጀራ የሚሰጥ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሔር ፍቅር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በልባችን እንደፈሰሰ ተናግሮአል። ሆኖም ግን ይህንን በልባችን የሰሰውን የእግዚአብሔርን ፍቅር በነፍሳችን ማስረፅ እና ብሎም በሙሉ ሃይላችን በመግለፅ ሁሉንም መውደድ ከእኛ ከሁላቸን የሚጠበቅ ክርስትያናዊ ግዴታችን ነው። በሌላ አባባልም ያለ ምክንያት ሌሎችን ለመወደድ አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን መቀየር መስዋዕት ከማቅረብ የሚበልጥ በኑሮ የሚገለጥ እውነተኛ አምልኮ ነው።
ስለዚህ በቤት ክርስትያን ውስጥም ሆነ በአገልግሎት ከምናቀርበው መስዋዕት ይልቅ አስቀድመን በእነዚህ ስድስት ወሳኝ በላጭ የኑሮ መስዋዕቶች ራሳችንን መፈተሽ በህልውናው ውስጥ ለምናቀርበው አምልኮ የማይነቃነቅን መሠረት ይጥሉልናል። በውጤቱም በዘመናችን ክብሩን አይተን የምናልፍበትን ፀጋና ማንም የማቋቋመውን ልዩ ቅባት ያስለቅቅልናል።
Share the Post:

Related Posts